የሕጉ የተፈጻሚነት ወሰን፣


ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው የጸረ ሙስና ልዩ ስነስርአትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 334/93 የአዋጁን የአፈጻጸም ወሰን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ አልነበረም፡፡ ይሁንና በተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ ስነስርአትና የማስረጃ ሕግ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 3 በፌዴራልና በክልል ተፈጻሚ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የሕጉ ተፈጻሚነትም በሙስና ወንጀሎች ላይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የሙስና ወንጀሎችን በተመለከተ ሕጉ ትርጉም የሰጠው ሲሆን፣ ይህም በወንጀል ሕጉ ላይ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ይሁንና ለምሳሌ ያህል በተሻሻለው የፌዴራል የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፣የኮሚሽኑን ስልጣን ሲገልጽ በወንጀል ህግና በሌሎች ሕጎች ውስጥ የተመለከቱ የሙስና ወንጀሎችን 18 ስለሚል፣ በሌሎች ሕጎች የተመለከቱትን የሙስና ወንጀሎች በሚመለከት 434/97 ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል ወይ?የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

1. አግባብ ያለው አካል


የሙስና ወንጀልን ለመመርመር ወይም ለመክሰስ የሚችለው ማን ነው? የሙስና ወንጀልን በሚመለከት አከራክሮ ውሳኔ ለመስጠት የሚችለው ማን ነው? በዚህ ክፍል ለአነዚህ ጥያቄዎች በህጉ የተቀመጠውን ምላሽ እንመለከታለን፡፡ በጸረ ሙስና የስነስርአትና የማስረጃ ህግ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 3 «አግባብ ያለው አካል» ማለት የሙስና ወንጀልን ለመመርመር እና /ወይም ለመክሰስ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው በማለት ይተረጉማል፡፡

ሙስናን ለመመርመርና ለመክሰስ አግባብ ያለው አካል ማንነው?


በፌዴራል ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 7(4) እንደተመለከተው በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ወይም ፌዴራል መንግስቱ ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ በክልል መስሪያ ቤቶች በወንጀል ህግና በሌሎች ህጎች የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች በመንግስት ሰራተኞች ወይም ባለስልጣኖች ወይም በሌሎች ሰዎች ስለመፈጸማቸው ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ኮሚሽኑ የመመርመር ወይም የመክሰስ ወይም እንዲመረመር ወይም እንዲከሰስ የማድረግ ስልጣን እንደአለው ያመለክታል፡፡2 በዚሁ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በአንቀጽ 8(2) ደግሞ ማንኛውም ወንጀልን ለመመርመር ስልጣን የተሰጠው አካል ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ምርመራ መጀመርና ለኮሚሽኑ ማሳወቅ እንደሚኖርበት ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም በአጭሩ ከጸረ ሙስና ኮሚሽን በተጨማሪ ማንኛውም ወንጀልን ለመመርመር ስልጣን ያለው የፌዴራልም ሆነ የክልል የምርመራ አካል የሙስና ወንጀልን መመርመር ይችላል ማለት ነው፡፡ 1. በአዋጁ አንቀጽ 8 እንደተመለከተው ሌሎች የምርመራ አካላት የሙስና ወንጀልን መመርመርን በተመለከተ ያላቸው ስልጣን በሁለት መልኩ ሊተይ ይችላል፡፡ 2. ኮሚሽኑ ለፌዴራልም ሆነ ለክልል ምርመራ አካላት የሙስና ወንጀልን እንዲመረምሩ ሙሉ ውክልና የሰጠ ከሆነ፣ የምርመራ አካላቱ እንደማንኛውም የወንጀል ጉዳይ ምርመራውን በማድረግ ምርመራውን ሲያጠናቅቁ በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ስልጣን ላለው አቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቡን ይልካሉ፡፡ 3. በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ውክልና ያልሰጣቸው የፌዴራልም ሆነ የክልል አካላት የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ መረጃ ከደረሳቸው ወይም በቂ ጥርጣሬ ካላቸው፣ ምርመራውን የመጀመር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይሁንና ምርመራ ስለመጀመራቸው ለኮሚሽኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ኮሚሽኑ ምርመራ የተጀመረበትን ጉዳይ ሲያውቅ፣ ጉዳዩ እራሱ ወስዶ ሊመረምረው ወይም ምርመራውን እንዲቀጥሉበት ሊወስን ይችላል፡፡ ይሁንና የምርመራ አካሉ የሙስና ወንጀል ምርመራ መጀመሩን ለኮሚሽኑ ሲያሳውቅ የጀመረውን ምርመራ ይቀጥላል፡፡ የምርመራ አካሉ የጀመረውን ምርመራ የሚያቆመው፣ ኮሚሽኑ እኔ እራሴ እመረምረዋለሁ፣ ወይም ሌላ አካል እንዲመረምር ውክልና ሰጥቻለሁና የምርመራ መዝገቡን አስረከብ ካለው ብቻ ነው ምርመራውን የሚያቆመው፡፡ የምርመራ አካሉ ምርመራ መጀመሩን ለኮሚሽኑ አሳውቆ፣ ከኮሚሽኑ ምላሽ ካልመጣለት፣ የመጀመረውን ምርመራ በማጠናቀቅ ስልጣን ላለው አቃቤ ህግ ይልካል፡፡ የሙስና ወንጀልን የመክሰስ ስልጣንን በሚመለከት የኮሚሽኑ ስልጣን እንደሆነ ከዚህ በላይ በተመለከተው ድንጋጌ የተመለከተ ሲሆን፣ ይሁንና ኮሚሽኑ እንደአስፈላጊነቱ ውክልና ለሌሎች አካላት ሊሰጥ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 9 ተመልክቷል፡፡ በፌዴራል መንግስቱ ለክልሎች ከሚሰጥ ድጎማ ጋር በተያያዘ የክልል ጸረ ሙስና ተቋም ወይም በክልሉ ሙስና ወንጀልን ለመክሰስ ስልጣን ያለው አካል ክስ መመስረት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይሁንና ኮሚሽኑ አስፈላጊ መስሎ ከታየው በቀጥታ በክሱ ውስጥ ሊገባ እንደሚችልም በአንቀጽ 9(2) ተደንግጓል፡፡

የዳኝነት ስልጣን

በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7 መሰረት የሙስና ወንጀልን የሚመለከቱ ማንኛውንም ጉዳዮች በሚመለከት የመወሰን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶችም የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1. የመንግስት ባለስልጣኖችን በተመለከተ በክልል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲሆን በፌዴራል የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡  የመንግስት ባለስልጣን የሚባሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከሚኒስትር በላይ የሆኑ ባለስልጣኖች፣ የቢሮ ሀላፊዎችና ከቢሮ ሀላፊዎች በላይ የሆኑ ባለስልጣኖች፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትረ ዴኤተዎችና ምክትል ሚኒስትሮች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ያካትታል፡፡ 2. የመንግስት ባለስልጣኖች ከሆኑት ውጭ ያሉትን የሙስና ጉዳዮች መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት በክልል የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን በፌዴራል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ 3. የዉጭ ሃገር አምባሳደሮችና ቆንፅላዎች እንዲሁም የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የዉጭ መንግስታት ወኪሎች ያሉበትን የሙስና ወንጀል መርምሮ የመወሰን ስልጣኑ የፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነዉ፡፡(አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8) የፍርድ ቤቶችን ስልጣን በተመለከተ ሕጉ በፌዴራልም ሆነ በክልል ለፍርድ ቤቶች ተሰጥተው የነበሩ አዋጆችን የሚያሻሽል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ በክልል ስልጣኑ የተሰጠው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚታዩ 21 የብርበራ፣ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይም ይሀው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው በመደረጉ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ጉዳዮች እንደሚያስተናግዱ ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃም ቢሆን የጊዜ ቀጠሮ የመሳሰሉት ጉዳዮች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚስተናገዱበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ለእነዚህ ጉዳዮች መከሰት አዋጁ በግልጽ ያላስቀመጠው መሆኑ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ከወንጀል ሕግና ሕገመንግስቱ የተከሳሾችን በተፋጠነ መልኩ ፍትህ ከማግኘት አንጻር በፍርድ ቤቶች እየተደረገ ያለውን ነገር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አስቸጋሪው ነገር በተለይ በክልል ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ያላቸው የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን በሚመለከት፣ ለሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች በክልል የሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤት ውክልና ያላቸው ፍርድ ቤቶች ለማየት ይችላሉ፡፡ ይሁንና ውክልና በሌላቸው ፍርድ ቤቶች ለምሳሌ በደቡብ፣ ጋምቤላ ወዘተ የሙስና ወንጀል ተፈጽሞ ቢገኝ ክሱ የት ይቀርባል የሚለውም ከህጉ አንጻር ስንመለከተው አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይም በክልል የብርበራም፣ የመያዝም የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይም ለክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሰጠቱ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል በመሆኑ በተግባር ሕጉ እየተተረጎመ አይደለም፡፡ ችግሮቹ በይበልጥ ጎልተዉ የሚታዩት ጉዳዩን ለመመልከት ስልጣን የተሰጠዉ ፍርድ ቤት ከሚያስችልበት የቦታ ርቀት፣በጥቆማ ደረጃ የሙስና ወንጀል መሆን አለመሆኑን ከመለየት ጋር እንዲሁም ሰልጣን በሌለዉ ፍርድ ቤት የሚሰጡ ትዕዛዛት ህጋዊ ዉጤት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እነዚህን ነጥቦች በመዳሰስ ችግሮቹን ለማሳየት ይሞከራል፡፡ ስልጣን የተሰጠዉ ፍርድ ቤት ከሚያስችልበት የቦታ ርቀት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች፣ ለማጓጓዝ የሚወስደዉን ጊዜ ሳይጨምር ማንኛዉም ተጠርጣሪ በተያዘ በ48 ሰዐታት ዉስጥ በአቅራቢያዉ ወደሚገኝ ፍርድ ቤት(በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረዐት ህጉ አገላለፅ በጣም አቅራቢያዉ ወደሆነዉ ፍርድ ቤት) ሊቀርብ እንደሚገባ በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 19/3 እና በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረዐት ህግ ቁጥር 29 በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ የተጠርጣሪን በአፋጣኝ በፍርድ ቤት የመጎብኘት መብት 22 (የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት) ማረጋገጥ መሆኑ ግልፅ ነዉ፡፡ ህብረተሰቡ የተጠርጣሪን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እንዲጠበቅ የመፈለጉን ያህል የተፈጸመዉ ወንጀል በምርመራ ተጋልጦ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡም ይፈልጋል፡፡ ይህን የህዝብ ፍላጎት ከማረጋገጥ አኳያ ፍርድ ቤቶች ሁለቱንም ፍላጎቶች በሚያማክል (ባላንስ ባደረገ) መልኩ መስራት እንዳለባቸዉ አያከራክርም፡፡ ስለሆነም አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት እንደቀረበ ፍርድ ቤቱ በዋስ ሊለቀዉ አልያም ለመርማሪዉ የምርመራ ቀነቀጠሮ በመፍቀድ በእስር እንዲቆይ ሊያዝ ይችላል(የወ/መ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 59/2/3)፡ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዉ በእስር ሆኖ ምርመራ እንዲጣራ ሲወስን ለዚህ ስራ የሚሰጠዉ ቀነቀጠሮ በአንድ በኩል የተጠርጣሪን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በሌላ በኩል ደግሞ መርማሪዉ የተፈጸመዉን የወንጀል ድርጊት በአግባቡ አጣርቶ አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል መሆን ይገባዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ የዳኞች እዉቀት እጅግ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠዉ ነዉ፡፡ ከላይ እንደተቀመጠዉ የሙስና ወንጀል ክሶች እና ከምርመራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሁሉ የሚታዩት በፌደራል ጠቅላይ ወይም ከፍተኛ ወይም በክልሉ ጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነዉ፣በዚህ መሰረት ለህዝቡ ቅርብ የሆኑ የመጀመሪያ(ወረዳ) ፍርድ ቤቶች ስልጣን የላቸዉም ማለት ነዉ፡፡ ስልጣኑ የተሰጣቸዉ ፍርድ ቤቶች ደግሞ በማዕከልና በዞን ከተማ ደረጃ ላይ ያሉ በመሆናቸዉ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ ወደነዚሁ ፍርድ ቤቶች እየተመላለሱ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ፣የብርበራ ወይም የመያዣ ወይም የንብረት ዕግድ ትዕዛዝ ማግኘት በተግባር ሲታይ ከላይ በተጠቀሱተ የህዝብ ፍላጎት ላይ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡

የሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን
የቅጂ መብት © 2016 አኢኢ. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው